አልፈራም


Tuesday, April 30, 2024

የሰው ልጅ በ እምነቱ

 

የሰው ልጅ በ እምነቱ ራሱን ሲቀጣ፣  

የራሱን ጉድጓድ ሞሶ እንዳበቃ፣...መሰላል ይሰራል ...

ከገባበት ጉድጓድ መልሶ ሊወጣ።  

Sunday, April 28, 2024

እንዲህ ነው ሳምንቱ ... ሕማማት

 

ሰኞ በለሲቱ ደረቀች ይላሉ ...

ጌታችን ቢረግማት፣  

ሳያገኝ ሲቀር .... ፍሬ ፈልጎባት።

ከኛም ፍሬ ሃይማኖት ... ጌታ እንዳያጣ ፣  

ወገባችን ታጥቆ ... መልካም ምግባር ያምጣ።

ጥያቄና መልሱ ... ማክሰኞ ነበረ፣

ጌታችን ሁሉንም ... ገልጦ ተናገረ።

አይሁድ ቅር አላቸው ...

አምላክ ነኝ ቢላቸው፣

ክፉ ስራቸውን ገልጦ ቢያሳያቸው፣  

ረቡዕ ቆረጡ ይሙት በቃ አሉ፣  

በቅናት ከሰሉ ... እጅግ ተቃጠሉ፣

ባካል ተገለጠ   ... ሐሙስ ትህትና

ጌታ እግር አጠበ ... ቸር አምላክ ነውና  

አርብ እለት ነበረ ... ጌታን የሰቀሉት፣

ሞቱስ ሕይወት ነበር ምስጢሩን ሳያውቁት።

በቀዳሚ ሰንበት መቃብር ቢያኖሩት፣

እሁድ ‘ለት ተነሳ እስቲ ምን ያድርጉት !!

Saturday, April 27, 2024

ቁጣና በረከት …

 ቁጣና በረከት … 

ምስኪኑ የሰው ልጅ 

መነጽር አድርጎ … ምድር ባፈራችው … 

ዕይታውን ስቶ … ትርጉም ተገልብጦ … ዓለም .. ጉድ ሰራችው… 

ሞቱን ሕይወት ብላ … ብትሰፍርለት ቆሎ … 

የሰው ልጅ ተሞኘ … በረከት ነው ብሎ … 

ድንገት ጉንፋን ብጤ … ቢይዘው ታመመ … 

የእግዚአብሔር ቁጣ ነው … ብሎ ደመደመ … 

….

በረከት አንዲት ናት … ያቺም …  ልጁን ማግኘት 

ቁጣውም አንድ ነው … እሱም … ልጁን ማጣት …. !

ሙታን

 Elegy … 

ሙታን ዛሬም አሉ …ሞተው ደረት መቺ … 

ዱላ የሚመዙ … ሕይወትን ተማቺ … 

ትንሳኤን ኮርኩመው … ፍቅርን የሚገርፉ …  

እንጸልያለን … 

እንማልዳለን … 

መዳንን ሳያዩ ..

ሕይወትን ሳያዩ … ከቶ እንዳይረግፉ !

እንዴት ማረኝ ልበል …

 እንዴት ማረኝ ልበል … 

በአብ ቀኝ በኢየሱስ … ሆነና ሰፈሬ፣

ከማመስገን በቀር … ጠፋብኝ ነገሬ። 

በሚያስደንቅ ፍቅሩ … በሞቱ ለወጠኝ፣

ሰው መሆን ተረሳ … ልጁም አደረገኝ። 

አሁን … 

የተማርኩ … ስለሆንኩ … በደል የሌለብኝ፣  

ከአፌ ቃል ጠፋ … መናዘዝ አቃተኝ።  

ከእቅፉ ገብቼ … ህልውናው ውጦኝ፣  

ባዲሱ ማንነት … እንዴት ልበል ማረኝ?

 

ምናልባት ጸሎቴ … ሕይወት እንዲበዛ፣  

አንድ ሰው እንዳይጎል … እንዲሁ እንደዋዛ። 

ይህቺን ጸሎቴም … ምናልባት ካስታጎልኩ፣  

በዚህ ዓለም ተውኔት … ምናልባት ከተሳብኩ። 


አንድ ጋት ተስንዝር … ቁልቁል ለመራመድ.፣ 

ያሰብኩኝ እንደሆን …  

ማረኝ እልሃለሁ … ተመልሼ እንዳልወርድ!!

ፍቅር ሞት ስትሆን … ሕይወት ፍቅር ሆነች፣

 Birth, Faith, Love 

ገና አራስ ሕጻን .. 

ከናቱ መሃጸን ሾልኮ እንደወጣ … እንዴት ተወለድኩኝ?

ብሎ ቢጠይቃት እናቱን በቅኔ፣ 

ፍቅር ቢዘንብብን … ባባትህ በእኔ… \

የዘጠኝ ወር አሳር ባንድ ቀን ተመዛ፣

ልትከስም ስትል የፍቅራችን ደብዛ፣ 

ተወልደህ ወለድከን … ፍቅራችንም በዛ።

Confusion … 

ያ ኣራስ ሕጻን አድጎና ጎልምሶ … 

እንዴት ተወለድኩኝ አለና ጠየቀ … ዳግም ተመልሶ። 

ከአምላክህ ፍቅር በዚህ የተነሳ፣ … 

ሞተና ወለደህ ከአዳም አበሳ፣ 

የምትለው ስብከት በፍቅር ሃሰሳ፣ ..

መልስ ልትሆን ቻለች …  

ፍቅር ሞት ስትሆን … ሕይወት ፍቅር ሆነች፣ 

በፍቅር ነው ብላ ያፈራች … መሃጸን በፍቅር መከነች። 

Enlightenment… 

ለካስ ፍቅር ማለት … 

ፍቅር የሆነውን ኢየሱስን ማግኘት !!

ለምን ለምን ሞተ ?! የሞተው ለኔ ነው !

 ለምን ለምን ሞተ ?! የሞተው ለኔ ነው !

TESFAYE HAILU B· APRIL 25, 2016· 4 MINUTE

ገባኝ ዝም ብዬ መስቀሉን አይቼ 

በፈሰሰ ደሙ ፈለግ ተመርቼ 

ፈለጉን ስከተል የደሙን ነጠብጣብ 

ቀራንዩ ደረስሁ ከመስቀሉ እርካብ 

ዐያለሁ ዐያለሁ መስቀሉን ዐያለሁ

ቀራንዬ ቆሜ መስቀሉን አያለሁ 

መስቀሉ ደም ለብሶ  

ችንካሩም ደም ጎርሶ 

ያበሳ ማህተም የሰቀቀን ቀለም ላዩ ታትሞበት 

በደንብ ያስታውቃል ጌታ እንደሞተበት 

እንዴት ለምን ሞተ አምላክ ሆኖ ሳለ 

ሰማይን የሰራው 

ምድርን የዘረጋው 

ለይኩን የሚለው .ያ ቃሉ እያለ

እኮ ለምን ሞተ … 

አምላክ ለምን ሞተ 

የአላዛር ትንሳኤ 

የሞት ሁሉ ጌታ 

እኮ ለምን ሞተ

ፀሐይ  እንድትጨልም 

ጨረቃ እንድትደማ  

መሬት እንድትዝል 

ኮከብ እንዲረግፍ … ከመሰለኝማ … 

አዚም ሸፍኖኝ ነው ….

ተረት ጋርዶብኝ ነው … 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለምስኪኑ 

ምስጢር ስተረትር … 

የሰው ህልም ስፈታ …

ለመሸብኝ ቀኑ … 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለጉስቁሉ … 

ፊደልን ሳዋድድ … 

ቅኔ ስፈበርክ … ለጠፋብኝ ቃሉ 

  

የሞተው ለኔ ነው 

አበሳዬን ሊያርቅ

ከገነት ሊያስገባኝ 

የሞላ ጎደለ ጫወታ ላዛለኝ 

ሃጢያት አኮስምኖኝ ጽድቄ ሁላ ጎድፎ 

ኢየሱስ በሞቱ አነሳልኝ ገፎ 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለድንብሩ 

አይዞህ ዘራፍ እያልኩ … 

ቀረርቶ እያሰማሁ ለጠፋሁ ከስሩ … 

የሞተው ለኔ ነው … ጉልበቴ ለከዳኝ 

ከዲብሎስ ፍልሚያ … 

ከሰይጣን ጦርነት ..በእጅጉ ላዛለኝ 

ሀይል ብርታት ሊሆነኝ … ፅድቄን ሊያሰምርንኝ 

ኢየሱስ አምላኬ … በፍቅር ሞተልኝ … 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለሰነፉ 

አለሁኝ ከቤትህ … 

አለሁ ከመቅደስህ … 

እያልኩ ለጠፋሁኝ … ሌሎቹም ሲጠፉ 

የመከራህ ቃላት ወንጌልህ ሲነገር 

መለኪያ የሌለው የፍቅርህ ዳር ድንበር 

መስማት እያቃተኝ … ሲቃ እያነቀኝ 

ለማን እንደምትሞት … 

ለምን እንደምትሞት … ነገሩ ሲገባኝ 

ሀዘን ከደስታ … 

ሀሴት ከምሬት ጋር … ድብልቅልቅ እያለ 

ልቤን ከጥግ ጥግ ያላጋት ጀመረ 

ለሞትህም ሙሾ … ለሞትህ እልልታ … 

አንተስ ትገርማለህ …ሁልግዜ ጌታ … 

የሞትከው ለኔ ነው … 

ግራ ቀኝ ለማላውቅ … ውሉ ለጠፋብኝ …

ገርበብ ያለ ሁሉ በሩን ለሚመስለኝ … 

እድሜዬን በሙሉ ሳንኳኳ ሳንኳኳ… እስኪላጥ መዳፌ 

ሞትህ በረገደው … እልልታ ላሰማ … ከሲኦል ባርነት ባንተ በመትረፌ 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለትንሹ 

ካፈር አበጅቶ … ነፍስን ለዘራብኝ … በቅዱስ ትንፈሹ …. 

የሞተው ለኔ ነው