አልፈራም


Tuesday, April 30, 2024

የሰው ልጅ በ እምነቱ

 

የሰው ልጅ በ እምነቱ ራሱን ሲቀጣ፣  

የራሱን ጉድጓድ ሞሶ እንዳበቃ፣...መሰላል ይሰራል ...

ከገባበት ጉድጓድ መልሶ ሊወጣ።  

Sunday, April 28, 2024

እንዲህ ነው ሳምንቱ ... ሕማማት

 

ሰኞ በለሲቱ ደረቀች ይላሉ ...

ጌታችን ቢረግማት፣  

ሳያገኝ ሲቀር .... ፍሬ ፈልጎባት።

ከኛም ፍሬ ሃይማኖት ... ጌታ እንዳያጣ ፣  

ወገባችን ታጥቆ ... መልካም ምግባር ያምጣ።

ጥያቄና መልሱ ... ማክሰኞ ነበረ፣

ጌታችን ሁሉንም ... ገልጦ ተናገረ።

አይሁድ ቅር አላቸው ...

አምላክ ነኝ ቢላቸው፣

ክፉ ስራቸውን ገልጦ ቢያሳያቸው፣  

ረቡዕ ቆረጡ ይሙት በቃ አሉ፣  

በቅናት ከሰሉ ... እጅግ ተቃጠሉ፣

ባካል ተገለጠ   ... ሐሙስ ትህትና

ጌታ እግር አጠበ ... ቸር አምላክ ነውና  

አርብ እለት ነበረ ... ጌታን የሰቀሉት፣

ሞቱስ ሕይወት ነበር ምስጢሩን ሳያውቁት።

በቀዳሚ ሰንበት መቃብር ቢያኖሩት፣

እሁድ ‘ለት ተነሳ እስቲ ምን ያድርጉት !!

Saturday, April 27, 2024

ቁጣና በረከት …

 ቁጣና በረከት … 

ምስኪኑ የሰው ልጅ 

መነጽር አድርጎ … ምድር ባፈራችው … 

ዕይታውን ስቶ … ትርጉም ተገልብጦ … ዓለም .. ጉድ ሰራችው… 

ሞቱን ሕይወት ብላ … ብትሰፍርለት ቆሎ … 

የሰው ልጅ ተሞኘ … በረከት ነው ብሎ … 

ድንገት ጉንፋን ብጤ … ቢይዘው ታመመ … 

የእግዚአብሔር ቁጣ ነው … ብሎ ደመደመ … 

….

በረከት አንዲት ናት … ያቺም …  ልጁን ማግኘት 

ቁጣውም አንድ ነው … እሱም … ልጁን ማጣት …. !

ሙታን

 Elegy … 

ሙታን ዛሬም አሉ …ሞተው ደረት መቺ … 

ዱላ የሚመዙ … ሕይወትን ተማቺ … 

ትንሳኤን ኮርኩመው … ፍቅርን የሚገርፉ …  

እንጸልያለን … 

እንማልዳለን … 

መዳንን ሳያዩ ..

ሕይወትን ሳያዩ … ከቶ እንዳይረግፉ !

እንዴት ማረኝ ልበል …

 እንዴት ማረኝ ልበል … 

በአብ ቀኝ በኢየሱስ … ሆነና ሰፈሬ፣

ከማመስገን በቀር … ጠፋብኝ ነገሬ። 

በሚያስደንቅ ፍቅሩ … በሞቱ ለወጠኝ፣

ሰው መሆን ተረሳ … ልጁም አደረገኝ። 

አሁን … 

የተማርኩ … ስለሆንኩ … በደል የሌለብኝ፣  

ከአፌ ቃል ጠፋ … መናዘዝ አቃተኝ።  

ከእቅፉ ገብቼ … ህልውናው ውጦኝ፣  

ባዲሱ ማንነት … እንዴት ልበል ማረኝ?

 

ምናልባት ጸሎቴ … ሕይወት እንዲበዛ፣  

አንድ ሰው እንዳይጎል … እንዲሁ እንደዋዛ። 

ይህቺን ጸሎቴም … ምናልባት ካስታጎልኩ፣  

በዚህ ዓለም ተውኔት … ምናልባት ከተሳብኩ። 


አንድ ጋት ተስንዝር … ቁልቁል ለመራመድ.፣ 

ያሰብኩኝ እንደሆን …  

ማረኝ እልሃለሁ … ተመልሼ እንዳልወርድ!!

ፍቅር ሞት ስትሆን … ሕይወት ፍቅር ሆነች፣

 Birth, Faith, Love 

ገና አራስ ሕጻን .. 

ከናቱ መሃጸን ሾልኮ እንደወጣ … እንዴት ተወለድኩኝ?

ብሎ ቢጠይቃት እናቱን በቅኔ፣ 

ፍቅር ቢዘንብብን … ባባትህ በእኔ… \

የዘጠኝ ወር አሳር ባንድ ቀን ተመዛ፣

ልትከስም ስትል የፍቅራችን ደብዛ፣ 

ተወልደህ ወለድከን … ፍቅራችንም በዛ።

Confusion … 

ያ ኣራስ ሕጻን አድጎና ጎልምሶ … 

እንዴት ተወለድኩኝ አለና ጠየቀ … ዳግም ተመልሶ። 

ከአምላክህ ፍቅር በዚህ የተነሳ፣ … 

ሞተና ወለደህ ከአዳም አበሳ፣ 

የምትለው ስብከት በፍቅር ሃሰሳ፣ ..

መልስ ልትሆን ቻለች …  

ፍቅር ሞት ስትሆን … ሕይወት ፍቅር ሆነች፣ 

በፍቅር ነው ብላ ያፈራች … መሃጸን በፍቅር መከነች። 

Enlightenment… 

ለካስ ፍቅር ማለት … 

ፍቅር የሆነውን ኢየሱስን ማግኘት !!

ለምን ለምን ሞተ ?! የሞተው ለኔ ነው !

 ለምን ለምን ሞተ ?! የሞተው ለኔ ነው !

TESFAYE HAILU B· APRIL 25, 2016· 4 MINUTE

ገባኝ ዝም ብዬ መስቀሉን አይቼ 

በፈሰሰ ደሙ ፈለግ ተመርቼ 

ፈለጉን ስከተል የደሙን ነጠብጣብ 

ቀራንዩ ደረስሁ ከመስቀሉ እርካብ 

ዐያለሁ ዐያለሁ መስቀሉን ዐያለሁ

ቀራንዬ ቆሜ መስቀሉን አያለሁ 

መስቀሉ ደም ለብሶ  

ችንካሩም ደም ጎርሶ 

ያበሳ ማህተም የሰቀቀን ቀለም ላዩ ታትሞበት 

በደንብ ያስታውቃል ጌታ እንደሞተበት 

እንዴት ለምን ሞተ አምላክ ሆኖ ሳለ 

ሰማይን የሰራው 

ምድርን የዘረጋው 

ለይኩን የሚለው .ያ ቃሉ እያለ

እኮ ለምን ሞተ … 

አምላክ ለምን ሞተ 

የአላዛር ትንሳኤ 

የሞት ሁሉ ጌታ 

እኮ ለምን ሞተ

ፀሐይ  እንድትጨልም 

ጨረቃ እንድትደማ  

መሬት እንድትዝል 

ኮከብ እንዲረግፍ … ከመሰለኝማ … 

አዚም ሸፍኖኝ ነው ….

ተረት ጋርዶብኝ ነው … 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለምስኪኑ 

ምስጢር ስተረትር … 

የሰው ህልም ስፈታ …

ለመሸብኝ ቀኑ … 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለጉስቁሉ … 

ፊደልን ሳዋድድ … 

ቅኔ ስፈበርክ … ለጠፋብኝ ቃሉ 

  

የሞተው ለኔ ነው 

አበሳዬን ሊያርቅ

ከገነት ሊያስገባኝ 

የሞላ ጎደለ ጫወታ ላዛለኝ 

ሃጢያት አኮስምኖኝ ጽድቄ ሁላ ጎድፎ 

ኢየሱስ በሞቱ አነሳልኝ ገፎ 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለድንብሩ 

አይዞህ ዘራፍ እያልኩ … 

ቀረርቶ እያሰማሁ ለጠፋሁ ከስሩ … 

የሞተው ለኔ ነው … ጉልበቴ ለከዳኝ 

ከዲብሎስ ፍልሚያ … 

ከሰይጣን ጦርነት ..በእጅጉ ላዛለኝ 

ሀይል ብርታት ሊሆነኝ … ፅድቄን ሊያሰምርንኝ 

ኢየሱስ አምላኬ … በፍቅር ሞተልኝ … 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለሰነፉ 

አለሁኝ ከቤትህ … 

አለሁ ከመቅደስህ … 

እያልኩ ለጠፋሁኝ … ሌሎቹም ሲጠፉ 

የመከራህ ቃላት ወንጌልህ ሲነገር 

መለኪያ የሌለው የፍቅርህ ዳር ድንበር 

መስማት እያቃተኝ … ሲቃ እያነቀኝ 

ለማን እንደምትሞት … 

ለምን እንደምትሞት … ነገሩ ሲገባኝ 

ሀዘን ከደስታ … 

ሀሴት ከምሬት ጋር … ድብልቅልቅ እያለ 

ልቤን ከጥግ ጥግ ያላጋት ጀመረ 

ለሞትህም ሙሾ … ለሞትህ እልልታ … 

አንተስ ትገርማለህ …ሁልግዜ ጌታ … 

የሞትከው ለኔ ነው … 

ግራ ቀኝ ለማላውቅ … ውሉ ለጠፋብኝ …

ገርበብ ያለ ሁሉ በሩን ለሚመስለኝ … 

እድሜዬን በሙሉ ሳንኳኳ ሳንኳኳ… እስኪላጥ መዳፌ 

ሞትህ በረገደው … እልልታ ላሰማ … ከሲኦል ባርነት ባንተ በመትረፌ 

የሞተው ለኔ ነው … ለኔ ለትንሹ 

ካፈር አበጅቶ … ነፍስን ለዘራብኝ … በቅዱስ ትንፈሹ …. 

የሞተው ለኔ ነው

እምነት ያለው ሰው አይፈራም …

 እምነት ያለው ሰው አይፈራም … 


ጦር ቢሰበቅ … ቢጎሰምም ሺኅ ነጋሪት 

ህዝብ በህዝብ ቢነሳሳ … ቢታጠቅም እልፍ ሰራዊት 

ሀገር መልኩ ቢደበዝዝ … ካርታው ቢፋቅ ከቀለሙ 

የማንነት ስር መሰረት … አይጎመዝዝ መቼም ጣሙ

የዘር ነገር ቢመትሩት … ቢለኩትም ቢጎትቱት 

ካዳም መቼም አልፎ አያውቅ … በወርቅ ሚዛን ቢመዝኑት 

ቃል ነው ና የጣር ዘመን መጀመሪው … ቸነፈሩ ያስተጋባው 

ህዝብ በ ህዝብ የተነሳው 

የጦር ወሬ የሚሰማው 

የሽብርወግ የሚናኘው … ካልሞቱት ነው አለን ብለው ከሚዋሹት፣ 

ወገኔ ሆይ … 

ከኛ መንደር ግን ሰላም ሞልቷል 

ከኛ መንደር አዳም ሞቷል፣ 

ዘርማንዘሩ አፈር በልቷል፣ 

አዲሱን ሰው ለብሰናዋል … እንደዚህ ነው የምናምነው፣ 

ለዚህም ነው የምንቆመው፣  

እምነታችን ኃይል ያደርጋል …. እኛም ደግሞ እናምናለን 

በአምላካችን በእግዚአብሔር … ከቤታችን ስለገባን፣

ምን አስፈራን !!  

ስለዚህ 

እምነት ያለው ሰው አይፈራም …

ሃገሬ ሰማይ ነው !

 ሃገሬ ሰማይ ነው !


የማለዳ አንቂ  … 

ያመርዶ ነጋሪ … ከቤቴ ቢመጣ፣   

ሲፈራ ሲተባ … 

ከደጄ ቆመና …  

በል ልበስ ተነሳ … 

ፊትክን አብስና .. ጋቢ ደርብና  

ከመደብ ተቀመጥ … እርም እንድታወጣ፡፡ 

ሀገርህ ሞታለች … 

በል ትፋ እርምህን … አንብቶ ሲያስነባኝ፣  

እርሱ ..እያለቀሰ ..እኔን ሳቅ ከጀለኝ፡፡  

ሀገሬ ሃገሬን  … ሲዘፍኑ ስሰማ፣ … 

ልቤ ልውስ ልውስ … ሆዴ ዠማ ዠማ፡፡ …  

የሚል ነበር ድሮ … 

ዘር የቆጠርኩ ቀን … ድንበር ያበጀሁ ለት …  

ተወኝ … አትንገረኝ … 

ሀገሬ ሌላ ነው .. አሁን ልረፍበት፡፡  

ወገን ድንበር ይሉት … 

ወንዝ ተራራ ጅረት …  

ሞትም ሆነ መሞት … 

ፓስፖርት የሌለበት …  

ከገቡ ተከፍተው … ከቶ እማወጡበት ..  

ሀገሬ ሰማይ ነው .. ግዛት የሌለበት …  

አንደኛው ባንደኛው ... የማይነሳበት፡፡

መኖር የሚቀለው …

 መኖር የሚቀለው …

ወዳጄ ሲያገኘኝ … በጠዋት በማታ፣   

ኑሮ እንዴት ነው ይላል … ሲሰጠኝ ሰላምታ፡፡ 

ኑሮ…  

ጠዋት ጭሮ… 

ማታ ሰፍሮ፣ 

ልክ እንደ ቄብ ዶሮ …

ወይ እንዳውራ ዶሮ …

ብዬ እንዳልመልስ … ሳቅ ይከጅለኛል፣

መኖር ኩንታል ሆኖ … መሸከም ከብዶኛል፡፡

ምን ልመልስለት … 

ጥሩ ነው ልበለው …. እንደወተሮ አፌ፣

በሃሰት ፈገግታ … ራሴን ቀጥፌ፡፡ 

ዛሬስ አልዋሸውም … ለእውነት ደፍሬ፣

መኖር አቅቶኛል … 

ጮኬ መለስኩለት … ደም ስሬን ገትሬ፡፡   

ወዳጄ ሳቀብኝ … እንባውን አፍስሶ፣ 

በመልሴ ተደንቆ … ደስታ ተላብሶ፡፡ 

ማን በተሸከመው … ማነው የሚማረር፤ 

ውሉ የጠፋባት … የዚች ዓለም ነገር፤ 

እርሱ ተሸክሞህ …. የህይወትህ ጌታ 

በምሬት አትመልስ … ስሰጥህ ሰላምታ፡፡ 

ወዳጄ 

መኖር የሚቀለው … 

የተሸከመህን … ያወቅከው እለት ነው፡፡

በሕልውናው ውስጥ … !! …

 በሕልውናው ውስጥ … !! … 

ያላለቀው መንገድ … ያልተፈታው ሕልሜ፣ 

ኑዛዜ ያልሻረው … ያልታደሰው ስሜ፣ 

ሁሌም ሃጢአተኛ … ክብር የጎደለኝ፣ 

ቀን መሽቶ ሲነጋ … አምና ላይ የምገኝ፣ 

ኃጢአት አሞጋሽ … ፈሪ ሰው ነበርኩኝ። 

እና … አንድ ቀን .. 

ለመሮር ስቃጣ … ለሞት ስንደረደር፣ 

በአደራ ልቤ … የብድር ሳፈቅር፣  

በእውነት የካብኩት … ውሸት ሆኖ ሲገኝ 

ያገኝሁት ሳይሆን … ያጣሁት አመመኝ። 

ከዛም … 

በሩን የከፈተው … የሚያስገባ ገብቶ፣  

የሌሎቹን ትቶ .. የሱን ሕይወት ሰጥቶ፣ 

ከሕልውናው ውስጥ …  ቢከተኝ ጎትቶ፣

ያላለቀው መንገድ … ያልተፈታው ሕልሜ፣ 

ኑዛዜ ያልሻረው … ያልታደሰው ስሜ፣ 

ባንዳፍታ ተረሳ … 

ዳር አልባው አበሳ።  

እና  

በህልውናው ውስጥ ለተሰወረ ሰው … 

መምሸቱም መንጋቱም ያው ለሱ አንድ ነው። 

ለሊት በሱ ብርሃን ደምቃለች ስላሉ፣ 

ቀን ሳትቀድመኝ ብሎ ከሷ መታገሉ፣ 

ዛሬ አከተመ!!  … ከኋላ ያለውን ከፊት ማባረሩ፣ 

በሕልውናው ውስጥ .. ሳይኖሩ እየኖሩ !!

COVER


 



መሄድና መምጣት

 መሄድና መምጣት 

፩. 

ወጥመድ ተሰበረ … ቅዠቱም ተፈታ፣ 

ሞራል ብርግድ ሲል … ጥያቄው በረታ። 

አጀንዳው ምንድነው … ነጥቡስ የቱ ነው? 

የትነው እምንሄደው እውነቱስ ከየት ነው? 

ማነው የጨቆነኝ ጭቆናስ ምንድነው? 

እያልን ስንጠይቅ … መልሱ ሁሉም ሆነ።  

፪.

እውነቱን እያወቅን ዓይናችን ተጋርዶ፣ 

ራስ ከእግራችን ባንድ ላይ ተገምዶ፣ 

ከተፈጥሮ እውነት … ብዙ ስለራቀ፣

የሰውልጅ ከራሱ … ራሱን ሰረቀ።

፫. 

መሃሉ ብርሃን መሃሉ ጨለማ፣

ራሱን ደብቆ ከውነት ሳይስማማ፣ 

ምስጢሩን ደብቆ .. ጠባሳውን ከቶ፣ 

ስሜቱንም ውጦ … ራሱንም ገቶ …

ሲወጣ ሌላ ነው … ሁሉን የሚወክል … ካባውም ዲሪቶ 

፬. 

ድራማው አንድ ነው … በእብደት የተኮላ፣ 

ውስጡ ባዶ ሲሆን … ውጪው እየሞላ፣ 

ይከታል ወደውስጥ … ሕይወቱ ተማርካ፣ 

በውድመት በጥፋት … ሚዛን እየለካ፣ 

፭. 

ታሪክ ስለሆነ … ሞራል መሰረቷ …. 

… እውነት የት አባቷ … 

ለመኖር ቢቃትት … ለውነት ቢሰናዳ፣

ሊሰብሩት ቢዘጋጅ … ሊታረድ ቢነዳ፣ 

አልገባ ስላለው …. 

በሰባራ ወጥመድ … መልሰው ሲከቱት.. 

ወጥመድ መስበሪያ ስልት … እዛ ውስጥ በራለት። 

አቤት !

ከ ኢየሱስ በቀር !!

 No lives matter … 

ከ ኢየሱስ በቀር !! 

ጥቁር ነብሱ ትብለጥ … ይከተላት ነጩ፣ 

እያለ ያውጃል … ዓለም ብልጭልጩ፣ 

አዋጁ የገባው … ሕይወት ያገኘ ሰው፣ 

የብርሃን ቀለም … ውስጡ የዘለቀው፣

ሲጮኹ አይጮህም … ያልፋል በአርምሞ፣ 

የሱን ሕይወት ክዶ … ባዲስ ህይወት ደምቆ … አምሮ ተሸልሞ። 

ነፍስም ሆነ ስጋ … መንፈስና ሕይወት፣ 

የንቧይ ካብ ከንቱ … ነው ጌታ ከሌለበት፣

ነፍሱን የካደ ሰው … ሕይወትን የሚዋጅ፣ 

በጥቁር በነጭም … ራሱን ሳይፈርጅ፣  

ብሎ ያመነ ሰው ..እኔ የእግዚአብሔር ልጅ፣  

ቀለም አልባ ነብሱን … በጌታው ሰውሮ፣ 

የኢየሱስን ሕይወት … በራሱ ላይ ገልጦ … በድፍረት መስክሮ፣ 

መኖር ያኮራዋል … በአብ ቀኝ ባማረ … ከልጁ ጋር አብሮ !  

መልካሙ እረኛ ድምጹን እያሰማኝ

 መልካሙ እረኛ ድምጹን እያሰማኝ፣

ከለምለም መስክ ላይ ወስዶ ቢያሰማራኝ፣ 

ዓይኔን ቀና ባደርግ …  

ምንደኛው እረኛ ምልክት ሲያሳየኝ፣ 

ድምጹ ተዘንግቶ ምልክቱ ሳበኝ፣ 

ተስቤ ተስቤ በግ መሆን አቃተኝ፣

በመመልከት ሳይሆን…  

በድምጽህ እንድኖር ጌታ አምላኬ እርዳኝ !!

ሕይወትና ኑሮ ሲቀላቀሉብኝ፣

 ሕይወትና ኑሮ ሲቀላቀሉብኝ፣

 

ሕይወት ከባድ ሆነ ኑሮ ተወደደ፣ 

እያልኩ አወራለሁ፣ 

ሕይወት የሆነኝን ውስጤ የገባውን

ሕይወቴን ካላየሁ። 

ሕይወቴን ሳየው ግን … ቃሉን ስፈትሸው፣ 

ኑሮም እንደእምነቴ … ሕይወቴም ጌታ ነው።  


“አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” ገላ 2: 20

ስሙ …

 ስሙ … 

እረኛው ሲመልስ … በጎች ሲጠይቁ፤

ብዙ ግዜ ኖረው…  

አሁን በተራቸው … በጎች ተጠየቁ፣  

መልስ ከየት ይምጣ …  

ጥያቄው ተረሳ … በጣም ተጨነቁ።

ጥያቄን መዘንጋት 

እንዴት መልስ ይሆናል ? 

የምትል ጥያቄ ልጠይቅ አስቤ … ፣

መልሱን ዘነጋሁት … ወይልቤ ውይልቤ …  

ጥያቄና መልሱን … የዘነጉ ለታ።

ዝም ብሎ መስማት… ከእረኛው ጌታ።

ደግሞ ደግሞ መስማት … ከእረኛው ጎታ።

ደግሞ ደግሞ መስማት … ከእረኛው ጎታ።

የ ኢየሱስ እንባ

 የ ኢየሱስ እንባ 

አምላክ ሆኖ ሳለ … የዓለማት ፈጣሪ፣ 

ወደ ፍቅሩ ዙፋን … በሩን ከፍቶ ጠሪ፣ 

እኔን በሱ አምሳል … ሰራኝ ስል አምኘ፣ 

በኔ አምሳል ሆኖ … ሲያለቅስ ተገኘ። 

እኔስ ያለቀስኩት … ለሞተው ወገኔ ፣ 

ሞትን ድል መንሳት …  ስላጣሁኝ ወኔ። 

እሱ ለአላዛር … ያለቀሰለት… ፣

እኔ እንደማልችል …

እሱ እንደሚችል … አምላኬ አውቆት!! 

በቃልህ ሞረደኝ … በቃልህ አበርታኝ፣ 

እለት እለት ሁሉ … አንተን ሆኜ ልገኝ፣ 

ወደዛች የ እምነት ጥግ … ኢየሱስ ውሰደኝ፣ 

ድካሜን እያሰብኩ … ሳልቅስ አልገኝ!!

ስራ አማረኝ !!

 ስራ አማረኝ !!

በልጁ ምህረት አዲስ የሆንኩት ሰው፤ 

በምን መስፈሪያ ነው እኔ እምለካው፣ 

በአምላክ ሕልውና በፈቃዱ ቅኝት እምራመደው ሰው፣ 

በዚህ ነው መንገዱ የሚለኝስ ማነው ፣ 

ሕይወትን ካገኘሁ በመንገዱ ከሄድኹ እውነቱም ከገባኝ፣ 

እኔ ካለሁበት ሰዎች እንዲገቡ መስራት ነው ያለብኝ፣ 

የሰማይ አምላኬ ክንውን ከሱ ነው፣ …  እኔ ተነሳሁኝ፣

ኢየሱስ እኔ ነኝ ወይስ ?

 ኢየሱስ እኔ ነኝ ወይስ ?

ኢየሱስ እኔን ነው ብዬ ስመሰክር ያደነቁኝ ሁሉ፣ 

ኢየሱስ እኔ ነኝ ብዬ ስመሰክር አንገት ይደፋሉ።

እስከ ጥግ ድረስ የወደደኝ አምላክ ሞቴን ተሸክሞ፣ 

ሞቱን ብሸከመው እኮ ምን ይደንቃል እኔ ዛሬደሞ። 

ኢየሱስ የሰውልጅ … እኔ ያምላክ ልጅ ነኝ … ብዬ እምፎክረው፣ 

ከማይጠፋው ብርሃን … ከማያልፈው መንግስት … ኢየሱስ ወስዶኝ ነው።

የኛ ልደት ጠፍቶ

 ስንፈልግ ውለን ስንደነቅ ከርመን አንድ ቀለም ጠፍታ፣ 

አምላክ ሰው መሆኑ ከሰው መወለዱ ምስጢሩ ሲፈታ፣ 

አምላክ ተወለደ ብለን ስንመሰክር እውቀቱን አገኘን፣ 

የኛ ልደት ጠፍቶ ዘመን አልባ ሆነን በሰማይ ተገኘን።

ብርሃን ነኝ I am Light

 am Light 

ሃሳብና ልቤ፣ በሥጋ አእምሮ፣ በሚጮህ ሹክሹክታ፣ ያልተበጃጀሁኝ፤   

ድቅቅ ካልኩበት፣ ከብናኙ ቅንጣት፣ አፈር ከሚሆነው፣ ቀርጸው ያላኖሩኝ፤

ወገኔ የምለው፣ የሚሞተው ፍጥረት፣ በሕግ በስራቱ፣ አስተምሮ ያልዳኘኝ፤ 

የሰራሁት ሃጢያት፣ በደልና ወድቀት፣ዘር እያስቆጠረ፣ ሰብሮ ያላሰረኝ፣  

ልቤን እያወከ፣ ወገቤን አጉብጦ፣ ያስነከሰኝ ሕመም፣ አፌን ያልሸበበኝ፣  

የብዥታ ሕመም፣ የማይደረስ ሕልም፣ የቀቢጸ ተስፋ  ቅዠት ያልነጠለኝ፤  

በልጁ በየሱስ በሰማሁት ወንጌል፣ ብርሃን መሆኔን ማወጅ የጀመርኩኝ፣ 

ባካል በስጋዬ ደክሜ ምታዩኝ፣ 

በመንፈስ የምደምቅ ዛሬ ብርሃን ነኝ !!

አልሸሽም …

 አልሸሽም … 


እሚሸሸው ሃጢያት … በደል አቃጣዩ፣ 

ሞትማ አይሸሽ … ድንገት ከች ባዩ። 

ነጭ እርግብ መጣና … ነገረኝ በጆሮ፣ 

ሞቴ መቃረቡን … ከአምና ዘንድሮ.፣ 

ሞት ሆይ አልሸሽህም … እጋፈጥሃልሁ፣ 

እንደ እየሱስ ስሆን አሸንፍሃለሁ !!

ለመሆን በመንገድ ላይ ……

ከመንገድ እንዳልቀር ጸሎታችሁ ይርዳኝ

ብስራተ አብ

 የ ዮሃንስ ወንጌል 

ከየኔታ’ግር ሥር … ከፊደል በኋላ… ድሮ ልጅ እያለሁ፣ 

ብስራተ አብ ብዬ … ወንጌል ቀጥያለሁ፣ 

ያኔ በንባብ ነው … በግዕዝ በ እዝል  … በአራራይ ዜማ 

የየሱስን ነገር … ሲተረክ ስሰማ፣ 

መች ገባኝ ነገሩ …

የ ሕይወት ሚስጥሩ … 

መንገዱ እውነቱ … 

የተፈታንበት … ከታሰርንበቱ፣ 

ብርሃን አይተናል በዚህ ቅዱስ ወንጌል፣ 

ብርሃን ውስጥ ገብተን ብርሃን ሆነናል፣ 

ከ እንግዲህ በኋላ ማን ይሸፍነናል።

ዓይኔ በርቶ

 የውስጥ ዓይኔ በርቶ ... የማየውም ካየኝ ... 

ምንጩ ጋ ከደረስኩ ... ቀድቶ መርካት እንጂ ... ከ'ንግዲህ ምን ቀረኝ ?

ታይቻለሁ ብዬ የማመኔ ምስጢር ፣ 

ብርሃን ነህ ብሎ ኢየሱስ ሲናገር፣ 

በጨለማ መሃል ብርሃን ስለሆንኩ፣ 

ታይቻለሁ ብዬ በ እምነት ተናገርኩ፣ 

የሚያየኝን እንዳየሁት የማየውም እኔን ካየኝ፣ 

ከእቅፉ መግባት እንጂ ... ከዚህ ዓለም ምንስ ቀረኝ ?

የዛ የወይን ግንድ

 የዛ የወይን ግንድ ... ገበሬው መልካም ነው፤ 

ቢቆርጥ ቢከረክም ... ሥራው ሁሌም ውብ ነው፤ 

ከዘለላው በፊት ... ገና ከግንዱ ላይ ... ትንሽ ጉጠት ሳለሁ ... በጣም ተጠንቅቆ፤ 

ቅርንጫፍ እንድሆን ... የፈቀደው እሱ ... እንዳፈራ አውቆ፤ 

ከራሴ የሚሆን ... የኔ ነው የምለው ... ከንቱ ቢሆን ጽድቄ፣  

እኔም ከግንዱ ጋር ይሔው ለዘለዓለም አለሁ ተጣብቄ፣ 

ገበሬውም ግንዱም ቅርንጫፍ ፍሬውም ሁሉምም በአንድነት 

እኔ እንዲገባኝ እኔን ለማስተማር የተጠቀመበት 

ወለል ብሎ ታየኝ ምስጋና ይብዛለት።

ባለአንድ መክሊቱ

 ባለአንድ መክሊቱ 


ለኔ ነው የሰጠው፣ ... አንዷን መክሊት መርጦ ...

አስር በተሰጠው ... አምስት በተሰጠው ... ከፍቅሩ ሳያጎድል ... እንደውም አብልጦ  

ዘርዝሬ ሳልበላት ... ወይ ሳልነግድባት  ... እንዲሁ አስቀምጬ  

ሌላው እንዳይወስዳት ... ቀብሬያት ከመሬት ... ሳልለውጣት ሸጬ 

እንዲሁ ደሃ ሆኜ ... አምላኬን ሳማርር ... እንዲገድለኝ ስመኝ ... ሰማይ ላይ አፍጥጬ 

አምጣ ያቺን መክሊት ... ሲለኝ ደጉ ጌታ ... በቁጣው መበርታት ... ባንኜ ደንግጬ 

ሳይዘራ የሚያጭድ ... ሳይበትን ሰብስቦ ... 

ጨካኝም መሆኑን ... ልቡናዬ አስቦ ... 

እነሆ መክሊትህ ... አልጠፋችም አለች ... ብየ ባስረክበው  

አውጡት ወዲያ ጣሉት  ... መክሊቱን ንጠቁት ... አስር ላለው ስጡት 

ብሎ ከመንግስቱ አስወጥቶ ጣለኝ ... 

አትርፎ ማይገኝ ... ሰነፍ ሃኬተኛ ... መሆኔ በደለኝ። 

አሁንማ ነቃሁ ... 

ዛሬ በምህረቱ ... ደግም ጠራኝና ... 

አንዱን ድንቅ መክሊት ... ልጁን ሰጠኝና ... 

በል ሂድ ተሰማራ ... ለዓለም ተናገር .. ይህን ወንጌል መስክር ...

እልፍ አኧላፍ አፍራ ... ትረፍና ብዛ  

በዚህ ድንቅ መክሊት ... የሰውልብን ግዛ !!

ብሎ ስላዘዘኝ ... 

ይኸው ለጌታዬ መልካሙ ባሪያ ነኝ!!

ቅኔለሞት


ስለሞት ነው የምቀኘው ... ድል ተነስቶ በትንሳኤ፣ 

ይደልዎ እንዲል ካህን ... በሕማም ገጽ በጉባኤ።

አንዴ ሞቼ በክርስቶስ ... ከ'ንግዲማ መቼ ልሞት፣ 

የልጁ ሕይወት በሕይወቴ ... ሥጋ ነፍሴን አረስርሶት፣

አርባ አንድዱን ኪራላይሶን ... ለምን ልቁጠር ተደፍቼ፣ 

በልጁ ሞት ስለሞትኩኝ ... በትንሳኤው ተነስቼ፣ 

ንሴብሆ ልበል እንጂ ... በብርሃኑ ተሞልቼ።

ዳግም ተነስተናል ...

 Tesfaye, [5/1/2022 5:42 PM]

ዳግም ተነስተናል ...

የኛ ትንሳኤማ ... ሞት ነበረው አሉ፣

አላዛርን እዩት ... እንዴት ቢባል ቅሉ ... 

ቃሉን ስለሰማን ... የኛን ሕይወት ክደን፣

በ እርሱ ሕይወትነት ... መኖር ከጀመርን፣

ዳግም ተነስተናል ... ሌላ ሞት የለንም ... 

አፈር ወደአፈር ... መሄዱ ባይቀርም !!!


Tesfaye, [6/11/2022 10:44 AM]

በዮሃንስ ወንጌል በ ፲፯ ኛው አስደማሚ ምዕራፍ 

ልቤ ተደመመ ቅኔን አፈለቀ በደስታ ዘረፈው ከመቅደሱ ደጃፍ  … 


ለአብ የነበርነው … ለወልድ ተሰጥተናል 

ሕይወት ስለሆነን …. ቃሉን ጠብቀናል 

ወልድ የያዘው ሁሉ 

የአብ እንደሆነ …. ጠንቅቀን አውቀናል 

ጌታም ስለእኛ …. መክበሩን አምነናል … 

ዓለም ገጭ ጓ ቢል … 

ከዓለም ሳንወጣ … በክንፎቹ ጥላ ከክፉ ተርፈናል 

ልጁን እንደጠላ … ዓለም ቢጠየፈን … ከቶ ምን ይደንቃል?

እኛም በክርስቶስ … ከአባቱ እልፍኝ … ላንወጣ ገብተናል 

ዓለም ሳይፈጠር … ለወልድ የተሰጠ … ያን ክብር አይተናል !! 

አሜን ተመስገን ነው ሌላ ምን ይባላል …

በዮሃንስ ወንጌል በ ፲፯ ኛው አስደማሚ ምዕራፍ

 በዮሃንስ ወንጌል በ ፲፯ ኛው አስደማሚ ምዕራፍ 

ልቤ ተደመመ ቅኔን አፈለቀ በደስታ ዘረፈው ከመቅደሱ ደጃፍ  … 


ለአብ የነበርነው … ለወልድ ተሰጥተናል 

ሕይወት ስለሆነን …. ቃሉን ጠብቀናል 

ወልድ የያዘው ሁሉ 

የአብ እንደሆነ …. ጠንቅቀን አውቀናል 

ጌታም ስለእኛ …. መክበሩን አምነናል … 

ዓለም ገጭ ጓ ቢል … 

ከዓለም ሳንወጣ … በክንፎቹ ጥላ ከክፉ ተርፈናል 

ልጁን እንደጠላ … ዓለም ቢጠየፈን … ከቶ ምን ይደንቃል?

እኛም በክርስቶስ … ከአባቱ እልፍኝ … ላንወጣ ገብተናል 

ዓለም ሳይፈጠር … ለወልድ የተሰጠ … ያን ክብር አይተናል !! 

አሜን ተመስገን ነው ሌላ ምን ይባላል …

ኢየሱስን ያዝኩት !!

 ኢየሱስን ያዝኩት !! 

ጠላቶች ሊገሉት ... ሊይዙት ፈለጉ፣ 

ወደሱ ቀረቡ ... እያፈገፈጉ፣  

ኑ ያዙኝ አለና ... 

በፈቃዱ ራሱን ... በጃቸው አኖረ፣ 

ይህን ታላቅ ምስጢር ... ማንስ መረመረ?  

እኔም ... 

ኢየሱስን ልያዝ ... ወገቤን ታጥቄ፣

መስቀል ተመርኩዤ ... ወንጌሉን ሰንቄ፣  

ልሰቅለው አይደለም ... ሕይወት ላረገው ነው፣ 

በኔ ፈቃድ ሳይሆን ... ሁሉ በሱ እኮ ነው። 

ኢየሱስ እንዲህ ነው ... 

አይደለም ልትይዘው ...

ልታምነው ስትፈልግ ... እሱ ካልፈቀደ፣ 

ያለሕይወት እምነት ... እያንገዳገደ፣

ሲቀርቡት ማፈግፈግ ... እየተለመደ፣ 

ስንት ዘመን ሄደ ... ስንት ቀን ነጎደ !!

በእምነት መኖር ነው ... እርሱን ሕይወት አርጎ፣

ሌላው ሁሉ ከንቱ ... ጌታን መያዝ በጎ።

እፎይ !

 እፎይ !

ሞቴን ከሞቱ .... ጋር ... ባደረገው ብዬ ... ተስዬ ነበረ፣ 

ቀን ቆጥሮ አልቀረም ... ልቤ ተከፈተ ... ስለቴም ሰመረ፣ 

አመንኩና ሞትኩኝ ... ይህን ዓለም ክጄ.. 

በሞቱም መሰልኩት 

የኔን ኑሮ ጥዬ ... ሕይወቱን ወስጄ ... 

በትንሳኤው እምነት ... 

ሕይወቴን ሰጠሁት.. 

ሕይወቴን ወሰደው ... ሞት ያለፈበትን ... 

ሕይወቱን ሰጥቶኛል ... 

የዘለዓለም እረፍት የነገሰበትን!!

ማህበራችንን አንተው !!

 ማህበራችንን አንተው !!


ክርስቶስ እኔ ነኝ ብዬ መናገሬ ... 

ለዝና አይደለም ለጉራና ወሬ ...

ከጉጉቴ ብዛት በፍቅሩ በፍቅሬ ...

በሚያስደንቅ ቃሉ በመንፈስ ሰክሬ ... 

ራሴን ከአብቀኝ በድንገት አግኝቼው ...

ማማ መወጣጫው ለካ መስቀሉ ነው ... 

ሞት የሚገባው ሰው በነጻ ተለቆ ... 

የማምይሞተው ሞቶ በኔ በደል ደቆ ... 

እኔን ስለሞተኝ ....  

ከመናገር በላይ ቃሉ ጠጥሮብኝ ... 

አምላክ እኔ ሆንኩኝ ...ከቶ እንዳይመስልብኝ!! 

አደራ !

እውነት እና ሃቁ ... ክርስቶስ እኔን ነው ... 

በፍቅር ተስቦ ... 

እርሱ እኔን ሆኖ ... ሞቴን ስለሞተ ... 

ሃጢያቴ በሱ ... ስለተከተተ .... 

ጻድቅ ሆኖ ሳለ ... አምላክም ፈጣሪ ... 

አምላክ ልሁን ሳልል ... የሁሉ ጀማሪ ... 

በሞቱ ልመስለው ... ጅምር ሰው ሆኛለሁ ... 

በቃሉ ታንጬ ... ሙሉ ሰው ለመሆን ... ጉዞ ጀምሪአለሁ

በትንሳኤው ቆሜ ... እርሱን መስያለሁ ... 

በአብ ቀኝ እንዳልሁ ... እርሱን ተመልክቼ ይህን አምኛለሁ። 

ይኼ ሁሉ እምነት ... የእንቧይ ካብ እንዳይሆን 

በምግባር በርትተን ... እንድንተናነጽ 

ቃሉን ምግብ አርገን ... በሕብረት እንሁን!!

አሁንም እዛው ነኝ ...

 አሁንም እዛው ነኝ ... 

ልጁ ከፍ አድርጎ ... 

ሕይወቱን ለግሶ ... 

ብርሃን አልብሶ ... ወዶ ካስቀመጠኝ ! 


ብዙ ነገር አለ ... 

ጎትቶ ለማወረድ ሁሌም የሚዳዳ፣ 

ስወጣ ስገባ በዚህች ዓለም ጓዳ። 

ስጋዬ ሲታመም ... ስራ ሲሰለቸኝ፣ 

መብላት መጠጣቱ ... ህልም ሲሆነብኝ፣ 

የበራልኝ መብራት ...  

ያገኘሁት ሕይወት ... በላይ ያስቀመጠኝ፣

እሱ ያጽናናኛል ... በዚህ ቆይ ይለኛል። 

ደግመው ከወረዱ ... 

ከዓለም ጉዳንጉዱ ፣ 

አንቆ የሚያስቀረው ... 

እልፍ አዕላፉ ነው።   


አሁንም እዛው ነኝ ... 

ልጁ ከፍ አድርጎ ... 

ሕይወቱን ለግሶ ... 

ብርሃን አልብሶ ... ወዶ ካስቀመጠኝ !