መሄድና መምጣት
፩.
ወጥመድ ተሰበረ … ቅዠቱም ተፈታ፣
ሞራል ብርግድ ሲል … ጥያቄው በረታ።
አጀንዳው ምንድነው … ነጥቡስ የቱ ነው?
የትነው እምንሄደው እውነቱስ ከየት ነው?
ማነው የጨቆነኝ ጭቆናስ ምንድነው?
እያልን ስንጠይቅ … መልሱ ሁሉም ሆነ።
፪.
እውነቱን እያወቅን ዓይናችን ተጋርዶ፣
ራስ ከእግራችን ባንድ ላይ ተገምዶ፣
ከተፈጥሮ እውነት … ብዙ ስለራቀ፣
የሰውልጅ ከራሱ … ራሱን ሰረቀ።
፫.
መሃሉ ብርሃን መሃሉ ጨለማ፣
ራሱን ደብቆ ከውነት ሳይስማማ፣
ምስጢሩን ደብቆ .. ጠባሳውን ከቶ፣
ስሜቱንም ውጦ … ራሱንም ገቶ …
ሲወጣ ሌላ ነው … ሁሉን የሚወክል … ካባውም ዲሪቶ
፬.
ድራማው አንድ ነው … በእብደት የተኮላ፣
ውስጡ ባዶ ሲሆን … ውጪው እየሞላ፣
ይከታል ወደውስጥ … ሕይወቱ ተማርካ፣
በውድመት በጥፋት … ሚዛን እየለካ፣
፭.
ታሪክ ስለሆነ … ሞራል መሰረቷ ….
… እውነት የት አባቷ …
ለመኖር ቢቃትት … ለውነት ቢሰናዳ፣
ሊሰብሩት ቢዘጋጅ … ሊታረድ ቢነዳ፣
አልገባ ስላለው ….
በሰባራ ወጥመድ … መልሰው ሲከቱት..
ወጥመድ መስበሪያ ስልት … እዛ ውስጥ በራለት።
አቤት !
No comments:
Post a Comment